Abstract:
የዚህ ጥናት አላማ አማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ማህበራዊ ትስስር
ሚድያን እንደ ቀውስ ተግባቦት ስልት አተገባበራቸው ምን እንደሚመስል መዳሰስ ነው፡፡
በጥናቱ አይነታዊና መጠናዊ የምርምር አቀራረብ ስልት ተግባራዊ ሲሆን መጠይቅ፣
ቃለመጠይቅ፣ድህረገጽ ዳሰሳና ምልከታ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ሆነው
አገልግለዋል፡፡ ኢላማዊ የናሙና አመራረጥ ዘዴ ተጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችንና ለቃለ-መጠይቅ
የዩኒቨርሲቲዎችን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሮች ለመምረጥ ተግባራዊ ሲሆን ይሁንታዊ
የናሙና አመራረጥ ዘዴ ደግሞ መጠይቅ ለሚሞሉ ተማሪዎች ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ሁነታዊ
የቀውስ ጊዜ ተግባቦት የጥናቱ ንድፈ ሀሳብ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚጠቁመው
አንደኛ ዩኒቨርሲቲዎች በአካባቢያቸው የክስተት ምልክቶች ቢኖሩም እንኳን ማህበራዊ
ትስስር ሚዲያውን በመጠቀም ከቀውስ በፊት የመከላከል ስራ ያልተሰራ ሲሆን በቀው ጊዜ
ደግሞ የቀውሱን ስፋትና ጥልቀት ለመቀነስ ሳይሆን ክስተት እንዳልተፈጠረ የማስተባበያ
መረጃዎችን ብቻ አስተላልፈዋል፡፡ ለዚህም ተጠቃሚው ወደ ማህበራዊ ሚድያ መድረክ
ወስዶ መወያያ አጀንዳ አድርጎ እንድወያይበት በር ይከፍታል፡፡ሁለተኛ የማህበረሰቡንና
የተማሪዎችን አመለካከት፣ አስተሳሰብና ግንዛቤ ለማሳደግ አወንታዊ ተጽእኖ ያላቸውን
ወቅታዊና አዳድስ እውቀቶችንና ቴክኖሎጅን ለማስተላለፍ ሳይሆን ለተቋሙ ገጽታ ግንባታ
ታሰቦ ልማታዊ መረጃዎችን ብቻ ይለጥፉበታል፡፡ ሶስተኛ ተማሪዎች ማህበራዊ ትስስር
ሚድያዎችን በተለይም ፌስቡክን በመረጃ ወቅታዊነዊነቱ፣ቅጽበታዊነቱና ብዝሃነቱ በልዩነት
የሚጠቀሙት ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በተቃራኒው በቀውስ ጊዜ መደበኛ ሚድያዎችን
በትኩረት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ይህ ደግሞ ተማሪዎች ለተለያዩ አሉባልታዎች ተጋላጭ
እንደሆኑ ያሳያል፡፡አራተኛ የቴክኖሎጅና የኢኮኖሚ እጥረት፣የበይነ መረብ ተደራሽነት
አለመኖር፣ የተጠቃሚዎች አመለካከትና ስሜታዊነት፣ብሄርተኝነት፣ የተማሪዎች መሰረታዊ
የሚድያ አጠቃቀም ክሂል አለመኖሩ፣ ግላዊነት፣ስምአልባነትና የዋይፋይ አገልግሎት ተደራሽ
አለመሆን ዩኒቨርሲቲዎች ማህበራዊ ትስስር ሚድያን እንደ ውጤታማ የቀውስ ጊዜ ተግባቦት
ስልት አድርጎ ለመጠቀም ተጽእኖዎች መሆናቸውን የጥናቱ ግኝት ይጠቁማል፡፡